You are on page 1of 6

Back to Front Page

የትግራይ ክልላዊ መንግስት መግለጫና አንድምታው።

ክፍል አንድ።

“እኛ የታገልነው እና መስዋዕትነት የከፈልነው ለሕግ የበላይነት ነወ”።

ዶ/ር ደብረፅየን ገ/ሚካኤል

በኅዳር 9 ቀን 2011 ዓ.ም (እኢአ) በትግራይ ክልላዊ መንግሥት ምክትል አስተዳዳሪ


እና የሕወሃት ሊቀመንበር በሆኑት በዶ/ር ደብረፅየን ገ/ሚካኤል የተሰጠውን ጋዜጣዊ
መግለጫ ክፍል አንድ በጥሞና አዳመጥኩት። ይህንን ጋዜጣዊ መግለጫ ያዳመጥኩት፤
ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ ተናገሩት የተባለውን በፌስ ቡክ ካነበብኩ በኋላ ነው።
ፕሮፌሰሩ፤ አሉ የተባሉትን በቀጥታ እሳቸው ከፃፉት ላይ ባላነብም፤ እሳቸው የተናገሩት፤
በብዙ የሕወሃት አክቲቪስቶች እየተራገበ ያለ ነገር በመሆኑ፤ ሃሳቤን ጣል አደርጋለሁ።
ፕሮፌሰር እንድርያስ ተናገሩ የተባለው፤ ዶ/ር ድብረፅየን ከተናገሩት፤ አንዳንድ ነገሮች ጋር
ጋር የሚመሳሰል ነገር ስላለው፤ በዚሁም ላይ አስተያየት እንድሰጥ ይፈቀድልኝ።

ዶ/ር ደብረፅየን፤ ጄኔራል ክንፈን በተመለከተ ስለተናገሩት ብዙ ነገር ተብሏል፤


የትግራይ ክልላዊ መንግስት፤ በዶ/ር ደብረፅየን አማካኝነት፤ ከሰጠው መግለጫ አደገኛ
የሆነውን እና ስህተት የሆነውን ነገር ከመተቸቴ በፊት፤ ከመግለጫው የወሰድኩትን እና
ብዙዎቻችን እንስማማበታለን ብዬ የምገምተውን፤ አዎንታዊ የሆነው ነገር ላይ ጥቂት
ልበል። ምንም እንኳን ዶ/ር ደብረጽየንም ሆኑ፤ የሚመሩት ድርጅት እና ክልላዊ መንግሥት
ሃሳባቸውን የማንፀባረቅ ሙሉ መብት ቢኖራቸውምና አንዳንድ ጉዳዮች ላይ የሰነዘሩት
ሃሳብ፤ ትክክለኛ እና ተገቢ ቢሆንም፤ የሞራል ሥልጣናቸውን ያጡበት ጉዳይ በመሆኑ፤
የማንንም ልብ ያሸንፋል ብዬ አልገምትም። በከፊል መግለጫው፤ “የምለውን አድርግ
እንጂ የማደርገውን አታድርግ” የሚለውን የፈረንጆቹን ብሂል ያስታውሰኛል።

Videos From Around The World


በድሮ ጊዜ የአሜሪካን ሕንዶችን (Native Americans) ከግዛታቸው ለማፈናቀል፤
ነጮች፤ ለሕንዶቹ የሃስት ቃል ይገቡላቸው እና፤ ያንን የገቡትን ቃል ስለማይፈጽሙ፤
ሕንዶቹ፤ ነጮቹን የማያምኑበት ደረጃ ላይ ስለደረሱ፤ ነጮች ሁለት ምላስ አላቸው (fork
tongue) ይላሉ፤ በእኛም ሃገር “በአንድ ራስ ሁለት ምላስ” እንደሚባለው ማለት ነው።
በአጭሩ፤ የትግራይ ክልል መንግስት መግለጫ፤ “በአንድ እራስ ሁለት ምላስ” ተብሎ
ሊቋጭ የሚችል ነው።

በዚህ ርዕስ በቀጣይ ተከታትይ ጽሁፎች፤ የክልሉ መንግስት ያነሳቸውን አንኳር


ጉዳዮች አነሳና፤ በተለይ፤ “የትግራይ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት” እንዳለ ለማሰመሰል
የተደረገው ሙከራ፤ በሕወሃት እና በክልሉ መንግስት ላይ የሚያደርሰውን የፖለቲካ ክስረት
ለማሳየት እሞክራለሁ። መግለጫው፤ የሕወሃት ባለስልጣናት፤ የትግራይን ሕዝብ
መሸሸጊያ ለማድረግ የቀጠሉበትን የፖለቲካ ቁማር ፍንትው አድርጎ ያሳየ ቢሆንም፤
ያነሳቸው በጎ ነገሮችም አሉት። ከአዎንታዊ መልዕክቶቹም ውስጥ፤ ክልሉ፤ “ለሕግ
የበላይነት እንደሚሰራ እና ሕገ መንግስቱ እንዲከበር” የበኩሉን ትግል እንደሚያደርግ
የገለፀው ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ’ ማንም የወንጀል ተጠርጣሪ፤ በፍርድ ቤት፤ በሕግ፤ ጥፋቱ
እስኪወሰንበት ወይም ፍርድ ቤት ወንጀለኛ ነው ብሎ እስኪፈርድበት ድረስ፤ ወንጀለኛ
ሳይሆን፤ “ተጠርጣሪ” መሆኑ እንዲታወቅ፤ መንግስትም የተጠርጣሪውን መብት
እንዲያከብር የሚለው ሃሳብ ነው።

ይህ አባባል፤ ብዙዊችን ያስደመመ እና ያስቆጣ ነው። ቁጣውም ተገቢ ነው።


ቁጣውን ተገቢ የሚያደርገው፤ እንዲህ ዓይነት አስተያየት፤ ላለፉት 27 ዓመታት የዜጎችን
መብት ይጥስ ከነበረ እና፤ እራሱ አርቅቆ በራሱ ጉልበት ያፀደቀውን ሕገ
መንግስት ከማያከብር የፖለቲካ ሃይል መነገሩ ነው። ይህ ቁጣ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አሁን
ባለንበት ደረጃ፤ ከሕወሃት/ከትግራይ ክልላዊ መንግስት፤ ይህ መባሉ፤ አዎንታዊ ገጽታ
አለው ብዬ አምናለሁ። ብዙዊቻችን፤ ላለፉት 27 ዓመታት ስንጮኽ የነበረው፤ ሕወሃት
መራሹ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲያቆም እና፤ ቢያንስ፤ እራሱ አርቅቆ
ያፀደቀውን ሕገ መንግሥት እንኳን እንዲያከብር ነበር። የሕወሃት መራሹ መንግስት ሕግ
እንዲያከብር በመጮህ ምክንያት፤ በአገር ቤት በነበሩ የፖለቲካ ታጋዮች እና ጋዜጠኞች ላይ
እስራት ብቻ ሳይሆን፤ አሰቃቂ የአካል ጉዳት እና ግድያዎች ተፈጽመዋል። ለበርካቶችም
መሰደድ ምክንያት ከመሆኑም በላይ፤ በስደት የምንገኘውም፤ በተለያየ ደረጃና መልኩ፤
“የግፍ ጅራፉ” አርፎብናል። ታድያ ዛሬ፤ ሕወሃት፤ ሕግ አከብራለሁ ሲል፤ እጃችንን እና
ልባችንን ከፍተን በመቀበል፤ የገባውን ቃል እንዲፈጽም ማስገደድ እና ሕግ ሲጥስ ተጠያቂ
ማድረግ ይጠበቅብናል። ይህ የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ነው። ከዚህ አንፃር ነው፤ የመግለጫው
አካል የሆነውን ፡“ሕግ እናከብራለን” “ሕግ ይከበር” የሚለውን የማየው።
አሁን የተጀመረው ጉዞ፤ ከዚህ በፊት ስንሄድበት ከነበረው የግጭት ፖለቲካ አዙሪት
የተለየ እንዲሆን ከፈለግን፤ “ትላንት እናንተ ስታደርጉት ነበር፤ ዛሬ ደግም በእናንተ ላይ
መደረግ አለበት” ከሚል የበቀል ድርጊትም ሆነ ስሜት መላቀቅ አለብን። በአሁኑ ሰዓት
የሚፈለገው፤ በቀል ሳይሆን ፍትሕ ነው። ከቆየንበት የፖለቲካ ባሕል አንፃር፤ ለብዙዊች
ይህንን መቀበል አስቸጋሪ እንደሚሆን ይገባኛል። ግን እነሱ (ሕወሃት እና አጋሮቹ)
ሲያደርጉት የነበረውን የሕግ ጥሰት ስናወግዝ የነበረን፤ አሁንም ሕግ ጥሰት ካየን፤ ጥሰቱን
ማውገዙን መቀጠል ይኖርብናል። አለዛ፤ እነሱ ሲስሩት ስህተት እኛ “የምንደግፈው” ኃይል
ሲሰራው ደግሞ፤ ልክ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ፤ መግለጫው በተደጋጋሚ ሕግ ይከበር
ማለቱ በአዎንታዊ መልኩ ሊወሰድ ይገባል።

ከዚህ በተጨማሪ፤ ከመግለጫው የሰማሁት በጎ ነገር፤ በቴሌቪዥን፤ በሜቴክ ላይ


የቀረበውን ዘጋቢ ፊልም (ዶክመንተሪ) መኮነኑ ነው። ይህም ተገቢ አቋም ነው። ሆኖም፤
ይህንኑ አሰራር የጀመረው፤ አሁን ተቃውሞ የሚያሰማው ቡድን መሆኑ ሊጤን ይገባዋል።
ዶ/ር ደብረፅየን፤ መንግስታቸው፤ ትላንት በእነ አርቲስት ደበበ እሸቱ ላይ “አኬልዳማ”
የሚል ዘጋቢ ፊልም (ዶክመንተሪ) ሰርቶ ለሕዝብ ማቅረቡን እና እነሱም እንዳጨበጨቡለት
የዘነጉትም ይመስላል። ይህ እነሱ የጅመሩት ዝርክርክ እና ሕገወጥ ስራ፤ ዛሬ መደገሙ
የሚገርም አይደለም። ምንም እንኳን በሃገሪቱ የለውጥ ሂደት ተጀምሯል ቢባልም፤ ለውጡ
ሙሉ ለሙሉ መንገድ ይዟል ማለት አይደለም። ትላንት የአኬልዳማን እና መሰል
“ድራማዎችን” ያወገዝን ሰዎች፤ በሜቴክ ላይ የተሰራውን ድራማ ልናወግዝ ይገባል። በዚህ
ረገድ የሕግ ባለሙያዎቹ ፍፁም አለሙ እና ሶልያና ሽመልስ በፌስ ቡክ ገጾቻቸው፤
የተጠርጣሪዎች መብት እንዲከበር ያሳሰቡት፤ እንደ ጥሩ ምሳሌ ሊወሰድ ይችላል። ከዚህ
ትምህርት በመውሰድ፤ ተጠርጣሪዎች፤ ሰሩ በተባሉት ወንጀል ሳይፈረድባቸው፤ ወንጀለኛ
ናቸው የሚል መደምደምያ በመንግስት አካላትም ሆነ በማንኛውም የሚድያ ተቋም
ሊነገር አይገባውም። በስሕተት ላይ ስሕተት መጨመር መፍትሔ አይሆንም። በበፊቱ
የሕወሃት መራሹ መንግስት አሰራር ከቀጠልንም፤ የምንፈልገው እና ብዙ መስዋዕትነት
የተከፈለበት፤ በሃገራችን የሕግን የበላይነት እውን የማድረግ ሂደቱ የተጨናገፈ ይሆናል።

ሌላው ከመግለጫው በአዎንታዊ መልኩ ያየሁት፤ ዶ/ር ደብረጽየን፤ በተደጋጋሚ፤


የእነጄነራል ክንፈ መታሰር ከእኛ ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር የለውም ማለታቸው ነው።
ጄነራሉም ሆኑ፤ ከደህንነት መስሪያ ቤቱ የታሰሩት ሰዎች፤ የፌደራል መንግሥቱ ቅጥር
ሰራተኞች እንጂ ከትግራይ ክልል መንግሥት ጋር የሚያገናኝ ምንም ነገር የላቸውም
ማለታቸው፤ ለአድማጩ፤ በጎ መልዕክት ያስተላልፈ ነው። በወንጀል ተጠርጠረዋል፤
ወንጀል ከሰሩ በሰሩት ወንጀል ይጠየቁ ማለታቸውም እሰየው ያሰኛል። መንግስት
የሚወስዳቸው እርምጃዎች ብሔር ተኮር እንዳይሆኑ፤ እንታገላለን፤ ይህንንም በገዥው
ፓርቲ የጋራ መድረክ ላይ በውይይት አንስተነዋል ሲሉም ተደምጠዋል፤ ይህ ጥሩ ነው። ለ-
44 ዓመታት ብሔር ተኮር እርምጃ ሲወስድ ከነበረ የፖለቲካ ድርጅት፤ ይህን መስማቱም
ተመስገን ያስብላል። ያ ማለት ግን ይህንን ያነሱበትን ምክንያት ሳናውቀው ቀርተን
አይደለም። ስናወግዘው የነበረውን ነገር ማውገዛቸውን ግን በአዎንታዊ መልኩ እንይ
ለማለት ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞም፤ መግለጫው፤ የተጀመረው ምርመራ በሜቴክ እና
በድህንነቱ መስሪያ ቤት ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር በተደጋጋሚ አሳስቧል። ይህም ይበል
የሚያሰኝ ነው። ከፌደራል መንግስቱም አልፎ፤ የክልል መንግስታት ባለስልጣናትም ላይ
ምርመራ እንዲደረግ፤ የትግራይ ክልሉ መግለጫ ይጠይቃል። በትግራይ ድብቅ እስር ቤቶች
አሉ ይባላል፤ እኛ እስከምናውቀው ምንም ድብቅ እስር ቤት የለም፤ የፈለገ ሃይል መጥቶ
ሊፈትሽ ይችላል ሲሉም ተደምጠዋል። በዚህ ላይ፤ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ተቃውሞ
የሚሰማ አይመስለኝም።

በእርግጥ እነዚህ አዎንታዊ የሆኑ ነገሮችን ከሚዛን ላይ ስናስቀምጥ፤ የመግለጫው


ዋና ዓላማ ይሄ ነው ወይ? ይህ የፖለቲካ ሃይል፤ በመግለጫው ይህንን፤ አብዛኛው
ኢትዮጵያዊ መስማት የሚፈልገውን ነገር ያካተትው ከእውነት ከመነጭ ፍላጎት ነው ወይ?
ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ መልስ ለማግኘት ብዙ መሄድ አያስፈልግም፤
መግለጫው። ምንም እንኳን አዎንታዊ የሆኑ ነገሮችን ቢያካትትም፤ እርስ በእርሳቸው
የሚጣረዙ፤ ክልሉ በበቂ ጭብጥ ሊከራከር የማይችልበት፤ አላስፈላጊ ወቀሳዎችንም
አደባልቋል። መግለጫውን በቅርበት ለመረመረው ማንም ሰው፤ መደምደምያው “በአንድ
እራስ ሁለት ምላስ” ሊሆን እንደሚችል ነጋሪ አያሻውም። ከላይ የጠቀስኳቸውን አዎንታዊ
ነገሮችን የሚጨፈልቅ በርካታ ነገሮችን መግለጫው ማካተቱ፤ ሊያሳስበን ይገባል።
መግለጫው፤ የፌደራል መንግስት ባለስልጣናትን፤ ጋዜጠኞችን፤ እንዲሁም ተቃዋሚ
የፖለቲካ ሃይሎችን ሲኮንን፤ በተለይ የሕወሃት መራሹ መንግስት ላለፉት 27 ዓመታት
በዚህች ሃገር ላይ ያደረሰውን ውድቀት መልሶ ማየት እንዳልቻለም፤ የሚጠቁም መግለጫ
ነው። በሃገሪቱ ስለተፈፀመው ዘረፋም ሆነ፤ ስለሰብአዊ መብት ጥሰት የምንናገረው፤
ከሚታይ እና ከሚዳሰስ ጭብጥ መሆኑ፤ ገና የተገለጠላቸው አይመስሉም ወይም፤ ሙሉ
ለሙሉ በክህደት ስነ ልቦና ውስጥ(Denial mode) የገቡ ይመስላሉ።

መግለጫው አስግራሚም ይዘቶች አሉት። በጥቂቱም ቢሆን፤ ላለፉት 27 ዓመታት


ሲገዙን የነበሩት ሰዎች፤ የጋዜጠኛ ሚና ምን መሆን እንዳለብት እምነታቸውን የሚያሳይ
መስኮትም ሆኖ አግኝቸዋልሁ። የክልሉ መንግስትም ሆነ ክልሉን የሚቆጣጠረው የፖለቲካ
ቡድን፤ ጋዜጠኞች በአንድ ሃገር ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባ ምን እንደሆነ ያልተገነዘበ፤
“ጋዜጠኝነት” ከሪፖርት አንባቢነት የዘለለ ሙያ መሆኑን የማያውቁ ሰዎች ስብሰብ ቡድን
መሆኑ፤ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪም ጭምር ነው። የክልሉ መንግሥትም ሆነ፤ የፖለቲካ
ድርጅቱ ለምርመራ ተኮር ጋዜጠኝነት (Investigative Journalism) “እንግዳ” መሆናቸውን
መግለጫው ያሳብቃል። መግለጫው፤ የጋዜጠኞች ሥራ ሪፖርት ማድረግ እንጂ ምርመራ
ማካሄድ አይደለም፤ ምርመራ የፖሊስ ስራ ስለሆነ፤ ጋዜጠኞች ያለሥራቸው መግባት
የለባቸውም ይላል። ይህ አውቆ አለማወቅ ነው ወይስ አለማወቅ? በአንድ ሃገር ውስጥ
ጋዤጠኞች ያላቸው ሚና፤ ተጽፎ የተሰጣቸውን ከማንበብ የዘለለ ነው። የጋዜጠኝነት ዋና
ሥራ፤ የመንግስትን ሃላፊዎችም ሆነ በሌላ የሃላፊነት እርከን ላይ ያሉ ሰዎችን ሥራ
“በምርመራ መነፅር” ማየት እና፤ ጉድለት ሲኖር ተጠያቂ ማድረግ ነው። የአሜሪካው
“የወተር ጌት ቅሌትም” ሆነ፤ ዛሬ በየቀኑ የምንሰማው “የትራምፕ ቅሌት” በምርመራ ተኮር
ጋዜጠኞች የተሰራ ነው። ስለዚህ፤ ጋዜጠኞች፤ ምንም እንኳን፤ ከፍርድ በፊት፤ እከሌ ወንጀል
ሰርቷል የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ ባይገባቸውም፤ የተሰሩ ወንጀሎችን፤ አብጠርጥሮ
የማውጣት እና ይህንንም ሕዝብ እንዲያወቅ ማድረግ የስራቸው አንዱ ሃላፊነት ነው።
ሜቴክ ውስጥ የተሰራውን ወንጀል፤ እንዲሁም በደህንነት መስሪያ ቤቱ የተሰራውን ግፍ
ማጋለጥ የጋዜጠኞቹ ሥራ ነው። በእርግጥ፤ ወንጀለኛው ይሄ ነው የማለት ሥልጣን
የላቸውም። ስለዚህ፤ የጋዜጠኛ ሥራ፤ ሪፖርት ከማንበብ ባሻገር መሆኑን ሕወሃትም ሆነ
የትግራይ ክልል መንግስት በቅጡ ሊረዳ ይገባል።

የትግራይ ክልል መንግስት መግለጫው ላይ አዎንታዊ ነገሮችን ያካተተው፤


አሉታዊ የሆኑትን እና ዋና እና መርዛም መለእክቱንም ለማድበስበስ ይመስለኛል።
የመግለጫው አንዱ አስገራሚ ነገር፤ የፌደራል መንግሥት፤ የወንጀል ተጠርጣሪዎችን
ከትግራይ ለመውሰድ፤ ከትግራይ ክልል ፈቃድ ማግኝት ያለበት ማስመሰሉ ነው። የፍርድ
ቤት ትዕዛዝ ካለ፤ ተጠርጣሪ ወንጀለኛን እናስረክባለን፤ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከሌለ ግን፤
ማንንም “አናስረክብም” የሚል መልዕክት ማካተቱ፤ ትግራይ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ
መንግሥት ሥር ነች ወይስ የራሷ ሃገር መንግስት ነች? ብሎ ለመጠየቅ የሚያስገድድ ነው።
እኔ እስከሚገባኝ ድረስ፤ በየትኛውም ሃገር የፌደራላው መንግስት አውቃቀር፤ የአንድ ሃገር
የፌደራል ፖሊስ፤ ፊደራል ነክ ወንጀል ከተሰራ፤ የወንጀሉን ተጠርጣሪ ለማሰር፤ የክልሉን
መንግስት “ፈቃድ የሚጠይቅበት” ምንም ምክንያት የለም። በብዙ ሃገሮች
እንደሚደረገው፤ የወንጀል ተጠርጣሪ ያለበት ካልታወቀ፤ ማንኛውም የክልል ሕግ አስከባሪ
ተጠርጣሪውን በመያዝ እንዲተባበር፤ የፌደራል ፖሊስ ወይም ዓቃቤ ሕግ ይጠየቃል።
ከዚህ በተረፈ ግን፤ የፌደራል ፖሊስ፤ የክልሉን መንግሥት ፈቃድ የሚጠይቅበት ምንም
ምክንያት የለም። በዚህ መልኩ፤ የክልሉ መግለጫ፤ በአንድ በኩል በወንጀል የተጠረጠሩ
ሰዎችን ለፌደራል ፖሊስ እናስረክባለን ሲል፤ በሌላ በኩል ደግሞ፤ በፌደራል ፖሊስ
የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎችን፤ ለመያዝ የፌደራል ፍርድ ቤት የእስር ትእዛዝ ማየት አለብን
ማለቱ መልእክቱ ምንድነው? እኔ የማውቀው፤ ሃገራችን በሕወሃት መራሹ ገዥ ቡድን ሥር
በነበረችበት ወቅት፤ የፌደራል ፖሊስ የትም ክልል ገብቶ እንደፈለገው ሲያስር እና ሲገድል
መቆየቱን ነው። ያ መቀጠል አለበት ማለቴ አይደለም፤ ግን፤ የፌደራል ፖሊስ “ተጠርጣሪ”
ያላቸውን ሰዎች ከየትም ክልል ሄዶ ሲያስር፤ የየትኛውንም የክልል መንግስት ፈቃድ
የሚጠይቅበት ሕጋዊ አሰራር ኖሮ አያውቅም። አሁን ታድያ የትግራይ ክልል አዲስ አሰራር
የሚጠይቅበት ምን ምክንያት አለው? ይህ ሕጋዊ መሰረት የሌለው፤ ለህወሃት ደጋፊዎች
ፖለቲካ ፍጆት የተወረወረች “ቀይ ሥጋ” ለመሆንዋ ምንም ጥርጥር የለኝም።

ሌላው የመግለጫው አንድምታ፤ በአሁኑ ሰዓት፤ በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩት


ሰዎች የታሰሩት፤ ለእስረኞች “ምህረት” ከተደረገ በኋላ በሰሩት ወንጀል መሆን አለበት፤
ምህረት ከመደረጉ በፊት ሰርተዋል በተባለው ወንጀል ተጠርጥረው ከሆነ የታሰሩት ግን፤
እነሱም በምህረት መፈታት አለባቸው፤ ይህ ካልሆነ ግን፤ ቀደም ብለው በምህረት የተፈቱት
ሁሉ ተመልሰው ወደ እስር መግባት አለባቸው የሚል ነው። ይህ በሕግ የበላይነት ሽፋን፤
የተሰነዘረው አደገኛ አስተሳሰብ፤ የገዥው ፓርቲ አካል ከሆነ የፖለቲካ ድርጅት የማይጠበቅ
ከመሆኑም በላይ፤ “እኛና እነሱ” በሚል መንፈስ ሕወሃት እስከዛሬ ሲያራምደው የነበረውን
የከፋፋይነት ፖሊሲ ቀጣይነት የሚያሳይ ነው። በአንድ በኩል፤ እኛ አያገባንም፤ እነዚህ ሰዎች
ወንጀል ሰርተው ከሆነ ስራቸው ያውጣቸው እየተባለ፤ በሌላ በኩል፤ ከሌሎች በግፍ
እና ያለምንም ሕጋዊ አግባብ ከታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች ጋር በማነፃፀር፤ ‘አሁን በወንጀል
ተጠርጥረው የታሰሩት “የእኛ ሰዎች ስለሆኑ”፤ ለሌላው ምህረት ስለተደረገ ለእነሱም
ምህረት ይደረግ፤’ የሚለው ሃሳብ፤ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ እንደማለት ይሆናል።
በዚህ ፀሃፍ እምነት “በምህረተ ተፈቱ የተባሉት የቀድሞ የፖለቲካ እስረኞች” መንግስት
እነሱን ይቅርታ መጠየቅ የነበረበት እና፤ ከመንግሥት ካሳ ማግኘት የሚገባቸው እንጂ፤
“መንግሥት ይቅርታ አደረገላቸው” በሚል ፌዝ ሊታለፍ የሚገባው አልነበረም። ሃገርን
በመመዝበር የተጠረጠሩ ሰዎች፤ ንፁሃን ዜጎችን ከሕግ ውጭ ያለአግባብ በማሰር፤ በእስር
የነበረን ሰው፤ ለሕሊና በሚከብድ እና በሚሰቀጥጥ መንገድ ሲያሰቃዩ የነበሩ ሰዎች፤
የሰውን ሕይወት ያለአግባብ እና ያለሕግ ሲቀጥፉ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን፤ በምህረት
ይለቀቁ፤ አለዚያም፤ “በምህረት ፈታናቸው ብለን ያፌዝንባቸውን ተበዳዮች” መልሰን
እንሰር ማለት፤ ሃላፊነት ከሚሰማው የክልል መንግስት የማይጠበቅ ብቻ ሳይሆን፤ ዛሬም
ሕወሃት፤ ከሰራው የግፍ ግፍ፤ ያልተማረ የፖለቲካ ሃይል መሆኑን የሚያሳይ ነው።

ክፍል ሁለት ይቀጥላል። Happy Thanks Giving!

Back to Front Page

You might also like

  • 2
    2
    Document1 page
    2
    Belayneh Tadesse
    No ratings yet
  • 12
    12
    Document2 pages
    12
    Belayneh Tadesse
    No ratings yet
  • 1
    1
    Document1 page
    1
    Belayneh Tadesse
    No ratings yet
  • 09
    09
    Document1 page
    09
    Belayneh Tadesse
    No ratings yet
  • Woy Zendero
    Woy Zendero
    Document4 pages
    Woy Zendero
    Belayneh Tadesse
    No ratings yet
  • Woy Zendero
    Woy Zendero
    Document12 pages
    Woy Zendero
    Belayneh Tadesse
    No ratings yet